Sunday, March 19, 2017

ደብረ ዘይት (የዐቢይ ጾም 5ኛ ሳምንት- መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም)

https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=586492778207221&id=212957815560721&substory_index=0
ደብረ ዘይት (የዐቢይ ጾም 5ኛ ሳምንት- መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም)
ደብረ ዘይት ማለት ቃሉ “ደብር” ሲል ተራራ ሲሆን “ዘይት” ሲል የወይራ ዛፍን ያመለከታል። ባጠቃላይ ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ (የዘይት ዛፍ) የበዛበት ተራራ ማለት ነው። ቦታው የሚገኘው በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ከጎለጎታ (ቀራንዮ) ተራራ በስተምስራቅ በግምት ፪ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው። በሁለቱ ተራሮች መካከል ጌቴሴማኒ የሚባለው ለምለም ስፍራ ይኸውም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመቃብር ስፍራ ይገኛል።
የደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ የሚያድርበት፣ የሚያስተምርበት፣ ውሎ የሚያርፍበት ሥፍራ ነው። ሉቃ 21፥ 37፣ ሉቃ 22፥ 39፣ ዮሐ 8፥ 1 ከዚሁ ተራራ ላይ ነው ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው። ኋላም በዳግም ምጽአት እዚሁ ተራራ ላይ ነው ለፍርድ የሚመጣው። /ሐዋ 1፥13/።
በደብረ ዘይት ተራራ ወገብ ላይ በሰፊው ተንጣሎ የሚታይ አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም የአይሁድ መቃብር ነው። ይህን ስፍራ ለመቃብርነት የመረጡበት ምክንያት ወደፊት መሢሑ መጥቶ እስራኤልን ነፃ አውጥቶ ወደ አባቱ ያርጋልና ኋላ ለፍርድ ሲመጣ በመጀመሪያ የሚፈርድበት ስፍራና ሙታንም የሚነሱበትና የሚሰበሰቡበት ስፍራ ይህ በመሆኑ እኛ መሢሐችንን ለማግኘትና ከሙታንም ለመነሳት የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን ብለው በማመናቸው ነው።
እንግዲህ በቤተክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት መሠረት የዓብይ ጾም እኩሌታ ደብረ ዘይት በመባል ተሰይሟል፤ ይኽውም በዚሁ ሰንበት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ስለዓለም ጥፋትና ስለዳግም ምጽአቱ ምልክቱን ነግሯቸዋል። ይኸውም /ማቴ. 24፥ 3-ፍጻሜ/ እንደተገለጸው፤
• ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ
• ጦርነትን የጦርነትንም ወሬ ትሰማላችሁ
• ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ
• በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም፣ የምድር መናወጥም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል
• በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል፤ ስለ ስሜም በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
• በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ
• ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ
• ከዐመፅም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች
• የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ታያላችሁ
• በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል ካለ በኋላ እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል በማለት ገልጾላቸዋል።
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር፡፡ ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበ አዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት፡፡
ትርጉም:- ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ተዘጋጅታችሁም ኑሩ፤ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ።ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ አላቸው፡፡ጌታችንም ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ በመለከት ድምፅ ከአእላፍ መላእክት ጋር በግርማ መለኮቱ ከሰማይ ወደ ምድር ይወርደል፡፡ በዚች ዕለትም ከሞተ ኃጢአት አብ ይማረን የሕይወት ባለቤት የሰንበትም ጌታ ነውና፡፡
ምንባባት መልዕክታት
(1ኛተሰ.4÷13-ፍጻ.) ወንድሞቻችን ሆይ÷ ስለ ሞቱ ሰዎች÷ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡ .......
(2ኛ ጴጥ.3÷7-14) አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል፡፡ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት÷ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡
ግብረ ሐዋርያት
(የሐዋ. 24÷1-21) በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት፡፡ ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ÷ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስተመሰገን አግኝተናታል፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
ምስባክ
መዝ. 49÷2 እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፡፡ ወአምላክነሂ ኢያረምም፡፡ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡
ትርጉም፦ እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡ አምላካችንም ዝም እይልም፤ እሳት በፊቱ ይነድዳል በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡
ወንጌል
(ማቴ. 24÷1-25) ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንጻ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡” (ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ: - ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ
በአጠቃላይ የደብረ ዘይት በዓል የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣት የምናስብበት፣ የመምጫው ምልክት የሆኑትን ነገሮች እየመረመርን ራሳችንን በንስሐ ሕይወት የምናዘጋጅበትና ከዘላለም ፍርድ ኩነኔ ለመዳን እንደ ቃሉ መመላለስ እንዳለብን የምናስብበት ነው። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁም ተብለናልና ሁልጊዜ ዝግጁና ስንዱ ሆነን እንደቃሉ ለመኖር እስከመጨረሻው ጸንተን ለመዳን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን!
ምንጭ ፡- የማህበረ ቅዱሳን ዋና ገጽ
የመላኩ እዘዘው የጡመራ ገጽ

No comments:

Post a Comment